Quantcast
Viewing latest article 9
Browse Latest Browse All 19

25 ታቦታትን የሚያስተናግደው የአቃቂ ቃሊቲ የጥምቀተ –ባህር ቦታ እያወዛገበ ነው

በ 

በጥብቅ የተፈጥሮ ስፍራነትና ከዘጠኝ አብያተ ክርስትያናት ለሚሰባሰቡ 25 ታቦታት ማደሪያነት ከ52 ዓመታት በላይ ሲያገለግል በነበረው የአቃቂ ቃሊቲ የጥምቀተ – ባህር ቦታ ላይ የከተማዋ የፅዳትና ውበት መናፈሻ ኤጀንሲ ለሌላ አገልግሎት ለመዋል እንቅስቃሴ መጀመሩ ቅር እንዳሰኛቸው ከዘጠኙ አብያተ ክርስትያናት የተውጣጡ ኮሚቴዎች ተናገሩ። “ልማትን ቤተክርስትያን አትቃወምም” ያሉት ኮሚቴዎቹ፤ ነገር ግን ቤተክርስትያናቱ ለዓመታት በጥብቅ የተፈጥሮ ስፍራነት ያቆየችውንና ለመንፈሳዊ አገልግሎት ስትገለገልበት የቆየችውን፤ የታቦታት ማደሪያና የጥምቀት ማከናወኛ ስፍራ በልማት ስም ከቤተ-ክርስትያን አካሄድ ውጪ ለሆነ ተግባር ማሰናዳት ተገቢ አይደለም ሲሉ የኮሚቴው ሰብሳቢና የቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ የሆኑት መልዓከ ፀሐይ አባ ሃ/መለኮት ይሄይስ በስፍራው ለተገኙ የሚዲያ ሰዎች ተናግረዋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ቦታው ለዓመታት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለና ከቤተ-ክርስቲያኗ ጋር በተደረገ ስምምነት የተጀመረ የልማት እንቅስቃሴ ነው ሲል ቅሬታውን ያስተባብላል። የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉነህ ፈይሳ አክለውም፤ “ልማቱን እያከናወነ የሚገኘው ክፍለ ከተማው ሳይሆን ከተማው ነው ያሉ ሲሆን፤ እንደአስተዳደር ጥያቄያቸውን ተቀብለን በከተማው ፅዳትና ውበት መናፈሻ ኤጀንሲ ጋር ተነጋግረው ከተማው ቢያለማውም የታቦት ማደሪያው ስፍራ እንደማይነካ ተማምነው የተጀመረ ስራ ነው ሲሉ” መልሰዋል።

የክፍለከተማ አስተዳደሩ ይህን ይበል እንጂ፤ ቤተ-ክርስትያኗም ቢሆን የከተማው ማስተር ፕላን በሚፈቅደው መልኩ ማልማት እንደምትችል ገልጻና ፕሮጀክትም አስገብታ እየተጠባበቀች ነበር ሲሉ የኮሚቴው አባላት ገልጸዋል። በአካባቢው የሚገኙ አብያተ ክርስትያናትና አድባራት ከ50 ዓመታት በላይ በሀገር በቀል እፅዋት ተንከባክበው ያቆዩትን የጥምቀተ- ባህር ስፍራ የቤተ-ክርስትያኗን አስተምህሮ በማይጋፋ መልኩ ለህዝብ መናፈሻ ይሆን ዘንድ በከተማው ማስተር ፕላን መሰረት ለማልማት በ1996 ዓ.ም ያቀረብነው ፕሮፖዛል ተቀባይነት ያገኘና አቅምም እንዳለን እየታወቀ የቤተ-ክርስቲያኗን ሥርዓተ ጥምቀት በሚጋፋ መልኩ እንቅስቃሴ መደረጉ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

ከተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች ባሳለፍነው ሐሙስ ጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ተገኝተው እንደተመለከቱት፤ የጥምቀተ ባህር ስፍራው እየተቆፈረና ግንባታም እየተካሄደበት ስለመሆኑ ተመልክተዋል። ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በተለያዩ ጊዜያት ደብዳቤዎችን ፅፈን አስገብተናል የሚሉት ከዘጠኙ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡት ኮሚቴዎች፤ “ነገር ግን መድረክ አመቻችተን ጠርተን እናናግራችኋለን ከማለት በስተቀር አሁንም ድረስ የመፍትሄ ሀሳብ ሳናገኝ ዓመታት አልፈዋል” ይላሉ። ተገቢው የመንግሥት አካል ጉዳዩን አውቆታል ብለን አናምንም የሚሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ አባ ሃ/መለኮት ይሄይስ፤ ፌዴራል ጉዳዮች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ማዘጋጃ ቤት በተደጋጋሚ መሄዳቸውን አስታውሰዋል። በተጨማሪም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በደብዳቤ ጉዳያችንን ብናቀርብም አሁንም መልስ አላገኘንም ይላሉ።

ይዞታው በከተማው አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ስር የሚገኝ ነው የሚለው የክፍለ ከተማው አስተዳደር፤ “የመንግሥትን ይዞታ መንግሥት ነው የሚያለማው” ሲሉም ይመልሳሉ። በከተማው ማስተር ፕላን መሠረት የሚገነባው መናፈሻ የጥምቀት ስርዓት ማከናወንን በፍፁም አያግድም፤ የተሰራው ፕላን ታቦት ማደሪያውን ግምት ውስጥ ያስገባ  ነው።  መንፈሳዊ ክንውኑም እንደወትሮው ይካሄዳል” ሲሉ የክፍለከተማው ሥራ አስኪያጅ ይመልሳሉ።

የአካባቢው ህብረተሰብ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እያሰማና እየታመሰ ይገኛል ያሉት የኮሚቴው አባላት፤ መድረካችንን ተጠቅመን ይሄነው ብለን ብንገልፅ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል በሚል በማረጋጋት ስራ ተጠምደናል ሲሉ የሚመለከተው አካል ጉዳያቸውን በትኩረት ተመልክቶ ይፋዊ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በአቃቂ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ስር የሚገኙት ዘጠኝ አብያተ ክርስቲያናት ደብረ ሰላም ቱሉ ዲንቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መንበረ ሕይወት መድሐኒአለም፣ ደብረፀሐይ ሳሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ጃጊ መካነ ሕይወት ኪዳነምህረት፣ ሰርቲ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም፣ መካነብርሃን ቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤል፣ ፋንታ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ሰጪ ቅድስት ማርያም እና ቀርሳ ቅድስት ልደታ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

ከጊዜ ወደጊዜ የአካባቢው ህዝብ ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ከግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው የሚሉት ኮሚቴዎቹ ከዘጠኝ አብያተ ክርስቲያናት የሚመጡ 25 ታቦታት የሚያድሩበት ይህ ስፍራ፤ ከዘጠኝ ወረዳዎች ለሚመጣ ህዝብ በጣም ጠቧል በሚባልበት ሁኔታ ሌላ ጫና የሚፈጥር ነገር ማከናወን ተገቢ አይደለም ሲሉ አስተዳደራዊ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።


Viewing latest article 9
Browse Latest Browse All 19

Trending Articles