Quantcast
Viewing latest article 10
Browse Latest Browse All 19

“Working on computer all day causes neck disc injuries”‹‹ኮምፒውተር ላይ ዓይን ተክሎ መዋል የአንገት ዲስክ ይጎዳል›› ዶክተር ብሩክ ላምቢሶ፣ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ኮንሰልታንት

ተጻፈ በ 

ዶክተር ብሩክ ላምቢሶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ኮንሰልታንት፣ እስፔሻሊስት፣ የአደጋዎች ሰብ ስፔሻሊስት፣ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የኢትዮጵያ የሕክምና ሥነምግባር ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስቶች ማኅበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የስፔሻላይዜሽን ፕሮግራም የተከታተሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን ሰብ ስፔሻላይዝ ያደረጉት ደግሞ በስዊዘርላንድ ነው፡፡ እንዲሁም አሜሪካ በሚገኙ ልዩ ልዩ የሕክምና አካዳሚዎች መገጣጠሚያዎችን በመቀየር፣ የአጥንት ሕክምናን በመምራትና መገጣጠሚያ ሳይከፈት በኦርትሮሲኮፒ ሕክምና መስጠት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን ተከታትለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች የታተሙ 25 የምርምር ጽሑፎችን ሰርተዋል፡፡ በአጥንት ሕክምናና በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ያጠነጠኑ ሁለት መጽሐፍቶችን አሳትመዋል፡፡ በአገር ውስጥ ደግሞ የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስቶች ማኅበር ባለፈው ዓመት ሁለት ሽልማቶችን አበርክቶላቸዋል፡፡ ከነዚህ መካከል አንደኛው ሽልማት “የዓመቱ ምርጥ የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት” የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የአጥንት ሕክምና ሂደት በጎ ተጽዕኖ የፈጠረ ምርጥ ሰርጂን” የሚሉ ናቸው፡፡ እንዲሁም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት በአቶ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአሥራ አንድ የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ከሻዕቢያ ጋር ባድመ ላይ በተካሄደው የመከላከል ውጊያ ላይ በሙያቸው ተሳትፈው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ እኝህን ከፍተኛ ባለሙያ በሕክምና ሥነ ምግባርና በአጥንት ቀዶ ሕክምና ዙሪያ ታደሰ ገብረ ማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሕክምና ሥነ ምግባር ኮሚቴ በአዋጅ የተቋቋመ ቢሆንም አንድ ሐኪም ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ ሙያዊ ቅጣት እንጂ ካሳ የማስከፈል ኃላፊነት የለውም፡፡ ለምን ? 

ዶ/ር ብሩክ፡- የሕክምና ሥነ ምግባር ብሔራዊ ኮሚቴ የተቋቋመው በአዋጅ ነው፡፡ የአባላቱም ስብጥር በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በወጣው መሠረት የተደረገ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከታቀፉት 19 አባላቱ መካከል አሥሩ ከስፔሻሊስት ማኅበራት የመጡ ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ አራቱ የሕግ ባለሞያዎች ሲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የላኳቸው በድምሩ አራት ተወካዮች እና የሕዝብ ታዛቢ የሆነ አንድ ታካሚ ይመደባል፡፡ ከዚህ ለመረዳት የሚቻለው ኮሚቴው የሚያሳልፈው የቅጣት ውሳኔ ሕጋዊነትን የተላበሰ መሆኑ ነው፡፡ ኮሚቴው ካሳ የማስከፈል ቅጣት ሊያሳልፍ አይችልም፡፡ ይህንን የማድረግ ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው ፍርድ ቤት ብቻ ነው፡፡ የሥነ ምግባር ቅጣት ማለት ካሳ ማስከፈል አይደለም፡፡ የሥነ ምግባር ግቡም ያጠፋውን ሐኪም አስተካክሎ፣ ሙያዊ ብቃቱን አሳድጎና እንደገና ወደ ሙያው ተመልሶ አገልግሎቱን እንዲቀጥል ማድረግ እንጂ አገር ጥሎ እንዲጠፋና በሚፈጠረው ክፍተት የሕክምና አገልግሎት ፈላጊው እንዲጉላላ ማድረግ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዋናው የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ሌላ በርካታ የስፔሻሊስቶች ማኅበራት አሉ፡፡ ይህ በሥነ ምግባር ክትትል ዙሪያ ችግር አያስከትልም? 

ዶ/ር ብሩክ፡- ከዋናው የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ሌላ ወደ 38 የሚጠጉ የስፔሻሊስቶች ማኅበራት አሉ፡፡ በጣም ከተጨመቀ ወደ 17 ይጠጋሉ፡፡ ሁሉም አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ አላቸው፡፡ የእነዚህ ጃንጥላ የሚሆነው ደግሞ አጠቃላዩ የሕክምና ማኅበር ነው፡፡ የትም አገር ያለው አሠራር ይኸው ነው፡፡ ስፔሻሊስት ማኅበራት ከስኮላርሺፕና ከአንዳንድ ነገሮች ጋር በተያያዘ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል የአሜሪካ የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት ማኅበር ወይ ስኮላርሺፕ ለመወዳደር አለበለዚያም ወረቀትህን እንድታቀርብ ከፈለገ ከአጠቃላዩ ማኅበር አጽፈህ ብትሄድ አይቀበልህም፡፡ ከአጥንት ሕክምና ስፔሻሊቲ ማኅበር አምጣ ነው የሚለው፡፡ ሁለተኛው አስገዳጅ ሁኔታ ደግሞ የስፔሻሊስት ማኅበራት አባላት እየበዙ በመምጣታቸው ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ስፔሻሊቲዎች በአገር ውስጥ በብዛት እየተሰጡ ነው፡፡ የአጥንት ስፔሻሊቲ ለ30 ዓመታት ሲሰጥ የቆየው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጀምረዋል፡፡ ሶዶ ሆስፒታል ደግሞ ሊጀምር ነው፡፡ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጠይቋል፡፡ በአጠቃላይ በሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከአምስት በላይ የአጥንት ስፔሻሊቲ ማሰልጠኛዎች ይከፈታሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ትልቁ ማኅበር የሚያደርገው ነገር አለ፡፡ ስፔሻሊቲዎችም የሚያደርጉት አለ፡፡ ዋናው ነገር በጋራና ተናቦ በትብብር መስራት ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ለሕክምና የሄደን ሰው እንደ ደንበኛ ሳይሆን እንደ ኬዝ የመመልከት ነገር በሐኪሞች ይስተዋላል፡፡ 

ዶ/ር ብሩክ፡- አንዳንድ ሐኪሞች ዘንድ የኮምኒኬሽን ወይም የመግባባት ክህሎት ችግር እንዳለባቸው የማይካድ ነው፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ይህንኑ ችግር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲያነሱት ተስተውሏል፡፡ ለሕክምና የሚመጣ ሰው የራሱ የሆነ ስሜት፣ ኃይማኖት፣ አመለካከት እና ባህል አለው፡፡ ሐኪሙ ይኼንን ሁሉ ባገናዘበ መልኩ መግባባት መቻል አለበት፡፡ እንደ ዱሮ እኔ ልወስንልህ፤ እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ የሚለው አይሰራም፡፡ ምክንያቱም ሰው ያነባል፣ ኢንተርኔት ያያል፣ ከየትም መረጃ ያገኛል፡፡ ለሕክምና የሚመጡ አንዳንድ ወገኖችም ስለ አንዳንድ በሽታ ከሐኪሙ በላይ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ደረጃውን በጠበቀ መልኩና በሚያግባባቸው ሁኔታ ማስረዳት ግድ ይላል፡፡ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚመጣውንም እንደ ኬዝ ሳይሆን ደምበኛችን ታካሚያችን በሚል ማየት ይኖርበታል፡፡ በሁሉም ሕክምና ትምህርት ቤት የተማርነውም በዚህ መልኩ ነው፡፡ ደንበኞቻችን ወይም ታካሚዎቻችን ነው የሚባለው፡፡

ሪፖርተር፡- ወንድ ሐኪም ተቃራኒ ፆታን ሲያክም ምን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባዋል? 

ዶ/ር ብሩክ፡- አንድ የወንድ ሐኪም ተቃራኒ ፆታን ሲመረምር ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው (ሴንሴቲቭ) የአካል ክፍሎች መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ታካሚዋ ልብሷን ውልቅልቅ አድርጋ ስትቀርብ ስሜት፣ ሆርሞኖችና ዕድሜ ሐኪሙ እንዲሳሳትና አላስፈላጊ ግንኙነት እንዲፈጽም ሊገፋፉ ይችላሉ፡፡ የዚህ ዓይነት የሥነ ምግባር ችግር ገጥሞናል፡፡ ሲመረመሩ የማይሆን ነገር የደረሰባቸው ሴቶች ክስ ያቀረቡበት ጊዜ አለ፡፡ በትምህርቱ መሠረት ለሕክምና የምትመጣ አንዲት ሴት በወንድ ሐኪም ስትመረመር አጠገቧ ተመሳሳይ ፆታ ያላትን ዘመድ ወይም ጓደኛ በፈቃዷ ማቆም አለባት፡፡ ይህ የማይገኝ ከሆነ ሐኪሙ ከሴት የሥራ ባልደረቦቹ አንዷን ማቆም ይኖርበታል፡፡ ግዴታም ነው፡፡ በሕክምናው በዚህ መልኩ የሚቆሙ ሰዎች ቻንረን (Chaneron) ይባላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የአጥንት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ያብራሩልን? 

ዶ/ር ብሩክ፡- የአጥንት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ወይም ኦርቶፔዲክ ሰርጂን የሚባል ስፔሻሊስት በዓለም  በጣም የታወቀና የጊዜው ጥያቄና መልስም የሆነ ትልቅ ሕክምና ነው፡፡ ምክንያቱም አደጋዎች፣ ጦርነቶች፣ ስብራቶች፣ እንዲሁም ከከተሜነትና ከኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የሰው መብዛትና የአደጋ ክስተት የቀን ተቀን ዜና እየሆነ መጥቷል፡፡ የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት የተሰበሩ ሰዎችን ይጠግናል፡፡ የሚጠገነውም አንዳንዶቹን በጄሶ ሲሆን አንዳንዶችን ደግሞ በኦፕራሲዮን አጥንቶቹን በሰው ብሎን በማሰር ነው፡፡ ይህ አይነቱንም ሕክምና የበለጠ ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎች ወደ አገራችን ገብተዋል፡፡ ከቴክኖሎጂዎቹም መካከል አንደኛውና በምኅጻረ ቃል ሳይን (SIGN) የሚል መጠሪያ ያለው መሳሪያ ይገኝበታል፡፡ በዚህ መሣሪያ አማካይነት የተሰበረውን ትልቅ አጥንት በመጠገን በሦስተኛውና በአራተኛው ቀን ታካሚው እንዲራመድና ወደ ሥራው እንዲሄድ ማድረግ ይቻላል፡፡ የተጠገነውም አጥንት ቀስ በቀስ እየዳነ ይሄዳል፡፡ ይህን ሕክምና ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን አገልግሎቱ በቅዱስ ጳውሎስ፣ በሶዶ፣ በጎንደር፣ በመቀሌ፣ በመቱ ሆስፒታሎች እየተሰጠ ነው፡፡ ሌሎቹ ቴክኖሎጂዎች ፕሌት እና ስክሩስ የሚባሉ ናቸው፡፡ እነዚህ መሣሪያዎች በሰው ብሎን አጥንት የሚታሰርባቸው ናቸው፡፡ አርትሮስኮፒ ደግሞ ሰውነት ሳይከፋፈት በትንሽ ቀዳዳ ተገብቶ በስክሪን እየታየ የፈራረሱና ያረጁ መገጣጠሚያዎችን ሙሉ በሙሉ ወይም በግማሽ እንዲቀየሩ ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- አጥንቶች በሰው ብሎን ከታሰሩ በኋላ ብሎኑ ይወጣል ወይስ እዛው ይቀራል? በታካሚውስ ላይ የጎንዮሽ ችግር አያስከትልም? በአገራችን በብዛት የሚታዩ የስብራት አደጋ ምንጮች የትኞቹ ናቸው? 

ዶ/ር ብሩክ፡- የሰው ብሎን የጎንዮሽ ችግር አያስከትልም፡፡ አንዳንዶቹ ጊዜያዊ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ የዕድሜ ልክ ናቸው፡፡ ጊዜያዊ የሆኑት ታካሚው ሲድን ይወጣሉ፡፡ ሦስት ዋና ዋና የስብራትና የአደጋ ምንጮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም መካከል 47 ከመቶ ያህሉ የመኪና አደጋ 18 ከመቶ ከማሽኖች ጋር የተያያዘ ሲሆን 18 ከመቶ ከሕንፃ ግንባታ ላይ በመውደቅ የሚደርሱ ናቸው፡፡ የቀረው በዱላና የመሣሪያ ድብድብ የሚመጣ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን በዱላና በመሳሪያ ድብድብ የሚደርሱ ስብራቶች ቀንሰዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአጥንት ኢንፌክሽንና ዕጢ ጋር በተያያዘ የሚሉን ነገር አለ? 

ዶ/ር ብሩክ፡– ለጥያቄህ መልስ ከመስጠቴ በፊት ልነግርህ የምፈልገው ነገር ቢኖር የዲስክ መንሸራተትና የአጥንት መሳሳትንም የአጥንት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት እንደሚያክም ነው፡፡ ከስፖርት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የአጥንት መሸማቀቅ፣ የሥር መዞር እንዲሁም ከማረጥ ጋር በተያያዘ በሴቶች ላይ የሚታዩ የአጥንት መሳሳት፣ የመገጣጠሚያ መሸርሸርንም ይኸው ስፔሻሊስት ሊያክም ይችላል፡፡ በተፈጥሮ አንድ ልጅ ሲወለድ እጅ ላይኖረው፣ ትርፍ ጣት ሊኖረው፣ ወረሃ ወይም ቆልማማ ሊሆን ይችላል፡፡ በተፈጥሮ ወይም በአደጋ የመዛነፍ፣ የመጣመም፣ የማንከስና የማጠር ነገሮች ሊኖሩት ይችላሉ እነዚህ የተጠቀሱት ችግሮች ሁሉ በቀዶ ሕክምና ሊስተካከሉ እንደሚችሉ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚህም ሌላ በገጠርና በከተማ የአጥንት ኢንፌክሽን ኃይለኛና ገር የሆኑ የአጥንት ዕጢዎች እንዳሉና የአጥንት ኢንፌክሽኑ ከከተማ ይልቅ በገጠር አካባቢ በሕጻናትና በልጆች ላይ እንደሚበዛ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ የገጠር ሕጻናትና ልጆች ከብት ያግዳሉ፡፡ ወደ ዱር ሄደው ማገዶ ይለቅማሉ፡፡ ከምንጭ ውኃ ይቀዳሉ፡፡ በአጠቃላይ ብዙ ሥራ ያከናውናሉ ይህን ሁሉ የሚሠሩት በብዛት በባዶ እግራቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሹል ነገርና እሾህ ይወጋቸዋል፡፡ ረመጥ ይረግጣሉ፡፡ ይህም ሲሆን ዘመናዊ መድኃኒት አይወስዱም፡፡ ባህላዊ መድኃኒት ይጠቀማሉ፡፡ ይህም ኢንፌክሽን ይፈጥራል፡፡ የተፈጠረውንም ያባብሳል፡፡

ሪፖርተር፡- የዲስክ መንሸራተት መንስኤው ምንድነው? 

ዶ/ር ብሩክ፡- የዲስክ መንሸራተት ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡ የመንሸራተቱ ዋንኛው መንስዔ ግን ከአኗኗር ባህሪ ለውጥ የተነሳ ነው፡፡ ብዙ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ አጭሯንም፣ ትንሻንም መንገድ በተሽከርካሪ መሄድን መምረጥና ረጅም መንገድ በእግር አለመሄድ ሌላው መንስዔዎች ሲሆን ከኑሮ ወጣ ውረድ የተነሳ ይመሻል፣ ይነጋል፣ ሁሌ ወደ ሥራ ሩጫ ነው፡፡ ማረፊያ ጊዜ የለም፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ይቆማል፣ ወይም ቁጭ ይባላል፡፡ ይህ ሁሉ ለዲስክ መንሸራተት መንስዔ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ኮምፒውተር ላይ ዓይን ተክሎ መዋል የአንገት ዲስክን ይጎዳል፡፡ በመቆም ደግሞ የወገብ ዲስክ ይታወካል፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አለመኖር ደግሞ ለበሽታው መስፋፋት መንስዔ ሆኗል፡፡ የዲስክ መንሸራተት ዱሮ የ19 እና የ20 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ታዳጊ ሕጻናት ላይ አይተን አናውቅም ነበር፡፡ አሁን ግን እያየን ነው፡፡ ሕጻናት የስፖርት እንቅስቃሴ አያደርጉም ላድርግ ቢሉም ቦታ የለም፡፡ የልጆች መጫወቻ ቦታ ማጣት ለዲስክ መንሸራተት መንስኤ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለስኳር ሕመም በሽታና ለውፍረት ዳርጓቸዋል፡፡ እንደው በአጠቃላይ በሰለጠነው ዓለም ከከተሜነት ጋር ተይይዘው የሚመጡና የምናያቸው በሽታዎች በአሁኑ ጊዜ በአገራችንም መጥተዋል፡፡ ዱሮ አንድ ሕጻን ላይ የስኳር በሽታ መኖር እንደ ጉድ ነበር የሚታየው፡፡ አሁን ግን የሕጻናት ስኳር በሽታ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ተለምዷል፡፡ እየበዛም መጥቷል፡፡ በአገራችን ከሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ የስኳር ሕሙማን ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የሆነበት ምክንያቱ ምንድነው? 

ዶ/ር ብሩክ፡– የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ከባድ ምግብ በመብላት፣ ኦርጋኒክ የሆኑትን እየተውን በፋብሪካ ፕሮሰስድ የሆኑ ምግቦችን ከሱፐርማርኬት እየገዙ መብላት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ማጣት፣ ቁጭ ማለት ማብዛት፣ የፌስ ቡክ፣ ቲቪ፣ ኮምፒውተሮችን ማብዛት ጌምን ማዘውተር ልጆቹን ይህንን ተወት አድርጋችሁ ለትንሽ ሰዓት ሩጡ፣ ተንቀሳቀሱ ለማለት ፈተና የሆነበት ጊዜ ላይ መድረሳችን ይህ ሁሉ ተጠቃልሎ ውፍረትን ያስከትላል፡፡ ውፍረት ደግሞ ዲስክ መንሸራተትን ያስከትላል፡፡ ዲስኩ 20 ኪሎ የሆነውን ልጅ የመሸከም አቅም እያለው የልጁ ኪሎ ግን 40 እና 50 ከሆነ ዲስኩ መሸከም ያቅተውና ይንሸራተታል፡፡ ዲስኩ ብቻ ሳይሆን መገጣጠሚያዎች ሁሉ ይጎዳሉ፡፡ የዳሌና የጉልበት ትልልቅ አጥንቶችም መሸከም እያቃታቸው ይሸረሸራሉ፡፡ በ70 እና በ80 ዓመት ዕድሜ የሚታየው ይህ ችግር ዛሬ ዛሬ 20 እና 30 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ወጣቶችና ታዳጊ ሕጻናት ላይ እየታየ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዲስክ ያረጃል?

ዶ/ር ብሩክ፡- በአገራችን አሁን ያለው የአንድ ሰው በሕይወት የመቆየት ዕድሜ ጣሪያ 64 ዓመት ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ላይ በሕይወት የመቆየት ዕድሜ ጣሪያ አሁን ካለበት ከፍ ይላል፡፡ ብዙ በኖርን ቁጥር በዛው መጠን ዲስኮችና መገጣጠሚያዎቻችን ሁሉ ያረጃሉ፡፡ ከአንገታችን እስከ “ጭራችን” ድረስ 33 ዲስኮች እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ዕድሜያቸው 60፣ 70 እና ከዛም በላይ የሆኑ ሰዎች ዲስክና መገጣጠሚያዎች ብዙ በመሥራታቸውና በማርጀታቸው መተካካት ያስፈልጋቸዋል፡፡ መተካትም የሚችሉ መለዋወጫዎች በአገራችን አሉ፡፡ እንደ ከዚህ በፊቱ ሕንድ፣ ታይዋን ወዘተ መሄድ አያስፈልግም፡፡ ያፈነገጠውን ዲስክ እናውጣውና አጠገቡ ያሉትን ሁለት አጥንቶች እናጋጥማቸዋለን፡፡ እነዚህን ሰርጀሪዎች ለመሥራት ብዙም አስቸጋሪ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከጥቂት ጓደኞችዎ ጋር ሆነው የአጥንት ሕክምና ብቻ የሚሰጥበት አንድ ትልቅ ሆስፒታል ለማቋቋም እየተንቀሳቀሳችሁ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንቅስቃሴው ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

ዶ/ር ብሩክ፡- ቦሌ አካባቢ “የመሥራቅ አፍሪካ የአጥንት ሪፈራል ማዕከል” አቋቁመናል በ5 ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ ላይ ያረፈና ባለ ስምንት ፎቅ የሆነው ይህ ማዕከል 120 አልጋዎች ይኖሩታል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት አገልግሎት ይጀምራል ብለን እናምናለን፡፡ እስካሁን ወደ 150 ሚሊዮን ብር ያህል ፈጅቷል፡፡ የመጀመሪያው ፎቅ የዲስክ መንሸራተት፣ ሁለተኛው ፎቅ የጉልበት፣ ሦስተኛው ፎቅ የዳሌ ችግሮች ያሉባቸው ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙባቸው ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ እስከመጨረሻው ፎቅ ድረስ የሴቶችና የሕጻናት ሙሉ ሕክምናን ጨምሮ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ስድስት የቀዶ የሕክምና ክፍሎች አሉት፡፡ ትልቅ ጅምና ፊዚዮቴራፒ አለው፡፡ ብዙ የመከላከልና አጥንትን የማጠንከር ትምህርትን እንሰጥበታለን፡፡ ሐሳባችን የታመሙ ብቻ ሳይሆን ጤነኞችም እንዳይታመሙ አስተምረናቸው እንዲጠቀሙበት ለማድረግ ነው፡፡


Viewing latest article 10
Browse Latest Browse All 19

Trending Articles