ኤርትራ ኢትዮጵያ በምታስተናግደው የመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮና (ሴካፋ)ላይ ከመሳተፍ እንዳልታገደች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ኤርትራ በሻምፒዮናው ታግዳለች በማለት ያስተላለፉት መረጃ ከእውነታ የራቀ ነው።
ቃል አቀባዩ ጉዳዩንም ”መሰረተ ቢስ” ብለውታል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ አገሪቱን ከሻምፒዮናው ማገድ እንደማትችል ገልጸዋል።
“ኤርትራ የተሳታፊ አገራት ዝርዝር ውስጥ አልተካተተችም፣ ለፌዴሬሽኑም ያቀረበችው ጥያቄ የለም” ብለዋል።
የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ተሳታፊ አገሮች ለተሳትፎ ጥያቄያቸውን ለሴካፋ እንደሚያቀርቡና ለአስተናጋጅ አገር ማቅረብ እንደማይችሉ አስረድተዋል።
ስለሆነም የተሳትፎ ጥያቄዋ በሴካፋ ተቀባይነት ሲያገኝ መካፈል እንደምትችል አመልክተዋል።
”አገሪቱ በቀጥታ ለኢትዮጵያ የተሳታፊነት ጥያቄ ብታቀርብ ተቀባይነት ልታገኝ አትችልም።ምክንያቱም አገሪቱ ትክክለኛውን ዲፕሎማሲያዊ ሂደት(ሴካፋ)ን ተከትላልትመጣ ግድ ይላታል” በማለት ፌዴሬሽኑ አለማገዱንም ኃላፊው አስታውቀዋል።
የኤርትራ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በሴካፋና በሌሎች በአህጉራዊና የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮናዎችና የማጣሪያ ጨዋታዎች ሳቢያ ከአገር ከወጡ ባለመመለስ ይታወቃሉ።
ምንጭ፦ ኢዜአ