አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገውን የሆቴሎች የኮኮብ ደረጃን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ተነስተዋል ።
ካለፈው አመት ጀምሮ በአዲስ አበባ ያሉ ሆቴሎችን የመመዘኑ ስራ በአለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅትና በኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሲሰራ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት የምዘናው የመጨረሻ ውጤት ይፋ ተደርጓል ።
ምዘናው 136 የአዲስ አበባ ሆቴሎች ለመመዘን አቅዶ ቢነሳም በሂደት የተመዛኞቹ ቁጥር ቀንሶና አንዳንድ ሆቴሎችም በደረጃ ምደባው ውስጥ ለመካተት ብቁ አይደሉም ተብለው ውጤቱ ይፋ ሆኗል ።
በዚህም መሰረት አራት ሆቴሎች ባለ አምስት ኮከብነት ደረጃን አግኝተዋል፤ የተቀሩትም ሆቴሎች በመመዘኛው መሰረት ደረጃ ተሰጥቷቸዋል ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች የደረጃ ምደባው መጀመር መልካም መሆኑን አንስተው፥ ይሁንና ሆቴሎቹ በደረጃው ውስጥ ለተቀመጡ መመዘኛዎች የተሰጠው የነጥብ አመዳደብ ያልተገባ ልዩነትን ፈጥሯል ይላሉ።
አቶ ግርማይ ረዳኢ በሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሆቴል ትምህርት ክፍል ሀላፊ ሲሆኑ፥ የሆቴሎች ደረጃ የወጣበትና ምዘናው የተጀመረበት ጊዜ ተመዛኝ ሆቴሎች እኩል ዝግጅት እንዲያደርጉ እድልን የሰጠ እንዳልነበር ነው የተናገሩት።
የተመዛኝ ሆቴል ህንጻ ደረጃ ዘመናዊ ወይንም አዲስ መሆን አንዱ መመዘኛ ሲሆን፥ ደረጃው የወጣው በ2006 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ነው፤ ምዘናው የተጀመረው ደግሞ አመት ሳይቆይ ነው።
ይህ መሆኑ ህንጻቸው አመታትን ያስቆጠረ ሆቴሎች ህንጻቸውን የማደሻ ጊዜ እንዳያገኙ ሲያደርግ፤ ይልቁንም በቅርብ የተሰሩ ሆቴሎች በዚህ መመዘኛ ጥሩ ነጥብን እንዲያገኙ እድልን መስጠቱን ነው አቶ ረዳኢ ያነሱት።
ለአብነትም ሂልተን ሆቴል በዚህ መመዘኛ አነስተኛ ነጥብ ማግኘቱንም ከዚህ ጋር ያገናኙታል ።
ለአብትነት በሆቴል ግቢ ውስጥ የመዋኛ ገንዳ መገንባት በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ኢንቨስትመንትን የሚጠይቅ ሆኖ ሳለ
በደረጃ አመዳደብ ውስጥ ግን የመዋኛ ገንዳ ከአስራ ሁለቱ መመዘኛ ርእሶች ውስጥ እንኳ አልገባም ።
የተመደበውም ተጨማሪ አገልግሎቶች በሚል አርዕስት ስር ሆኖ የሚያስገኘው ነጥብም በአንጻሩ አነስተኛ ገንዘብን ከሚጠይቁ አቅርቦቶች ያንሳል ።
በተጨማሪ በሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋም መምህር የሆኑት አቶ ግርማይ እንደሚሉት የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ትልቅ ኢንቨስትመንትን ይጠይቃል፤ ይሁን እንጂ በሆቴሎች ውስጥ ከአቅጣጫ አመላካች ጽሁፎች ብዙም ያልበለጠ ነጥብን እንዲያስገኝ ነው የተደረገው።
አቶ ግርማይ አሁን የተደረገው ምደባ ለኢንቨስትመንት የሰጠው ቦታ አነስተኛ መሆኑ እንደ ሂልተን ያሉ ሆቴሎችን እንደ ጎዳ ጠቅሰው፥ ይህ ሆቴል በውስጡ ያሉት በርካታ የመገበያያ ስፍራዎች የተሻለ ነጥብ ሊያስገኝለት ይገባም ነበር ብለዋል።
ይህም በአመዳደብ ላይ ክፍተት መኖሩን ያመላከተ መሆኑን ማየት ይቻላል ነው ያሉት።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ታደሰ እንዳይላሉ፥ የተባለው ነጥብ ብቻውን ደረጃውን የመወሰን አቅም የለውም፣ መስፈርቱ የተሰራው ሆቴሎችን ለማበላለጥ ቢሆን እንኳ ይህ ብቻውን የሆቴሎችን ደረጃ መወሰን አይችልም ብለዋል ።
አቶ ታደሰ አንድ ሆቴል መዋኛ ገንዳና ፓርኪንግ ስላለው ባለ አምስት ኮከብ አይሆንም፣ ስለሌለውም ብቻ ከዛ አይወርድም ይላሉ ።
በአንፃሩ የሆቴል ዋና መመዘኛ የሆኑት ምግብ፣ መጠጥና ማደሪያ እንደሆኑና ለእነሱም በምዘናው ትልቅ ስፍራ መሰጠቱንም ነው የተናገሩት።
የሂልተን ሆቴል ቀደም ሲል የአራት ኮከብነት ደረጃን አግኝቶ ይሁን እንጂ ቅሬታን ሲያቀርብ በድጋሚ ተመዝኖ ሶስት ኮከብ ደረጃን እንዳገኘ ተደርጎ የተናፈሰው ወሬም ከእውነት የራቀ መሆኑን አቶ ታደሰ ገልፀዋል።
ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ሆቴሎች ሲመዘኑ የተጠቃሚዎች አስተየያት በናሙናነት እንደ አንድ መመዘኛነት ቢወሰድ መልካም ነው የሚል አስተያየታቸውን ቢሰነዝሩም ይሁንና አቶ ታደሰ ይህ አለምአቀፍ አሰራር ባለመሆኑ አላደረግነውም ብለዋል ።
ሂልተን የሆቴሎች እና ሬዞርቶች ግሩብ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ኩባንያ ስሙን የማከራየት ልማዱ አራት እና ከዚያ በላይ ኮከብ ላላቸው ሆቴሎች ብቻ መሆኑ በምደባው የሶስት ኮከብነት ደረጃን ካገኘው ሂልተን አዲስ አበባ ሆቴል ጋር የነበረውን የስም ማከራየት ኮንትራት ሊያቋርጥ እንደሚችል ተነግሯል።
ይህም በኢትዮጵያ ለጊዜውም ቢሆን ትልቅ የንግድ ምልክት ያለውን ሆቴል እንዳያሳጣት ነው የተሰጋው።
በካሳዬ ወልዴ